ፒቡን ተዋወቁዋት - የመልኮሚያ ተረት አግኚ
ስለፒቡ ለወላጆች የተፃፈ መግቢያ
7/8/20241 min read


የጠዋቷ ፀሐይ የቤቶቹን ጣራ ወርቃማ ቀለም የምትቀባበት፣ ሳቅ እንደ ዕጣን ጢስ የሚወጣበት፣ ብሩህ እና ተስፋ በሞላበት 'መልኮሚያ' በሚባል ትንሽ መንደር ውስጥ፣ ባለ ሹሩባ እና ልቧ በድንቅ ነገር የተሞላች አንዲት ልጅ ትኖራለች። ስሟ ፒቡ ነው — እና እሷ የመልኮሚያ ታሪክ አግኚ ነች።
ፒቡ ተራ ልጅ አይደለችም። በአፍሪካዊ ቀለማት እና ንድፎች በተሸመኑ ለስላሳ የሐበሻ ጨርቆች የምትለብስ፣ የቤቷን ሙቀት እና የዕውቀት የማወቅ ጉጉትን ወደሄደችበት ሁሉ ይዛ የምትሄድ፤ መመርመር፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና በተራ ነገርሮች ውስጥ የተደበቀውን ድንቅ ነገር ማግኘት የምትወድ ልጅ ናት።
የእሷ ቋሚ ጓደኛ — እና አልፎ አልፎ ራስ ምታት የሚሆንባት — ቀዮ የተባለው ጎበዝ የኢትዮጵያ ተኩላ ነው። ተኩላ መሆኑ ከመታወቁ በፊት ቀይ ቀበሮ ይባል ስለነበረ ነው ፒቡ "ቀዮ" የሚለውን ስያሜ ያወጣችለት። ቀዮ ፈጣን አእምሮ ያለው፣ ድራማዊ፣ እጅግ ታማኝ እና አስተያየቱን ለመካፈል ፈጽሞ የማያፍር ነው። እሱና ፒቡ አብረው አብዛኛውን ቀናቸውን ያሳልፋሉ፦ በሳር ሜዳዎች ውስጥ ይሮጣሉ፣ ከእንቆቅልሽ እስከ ኃላፊነቶች ድረስ በሁሉም ነገር ላይ ይከራከራሉ፣ ማን ትክክል እንደሆነ ይጨቃጨቃሉ፣ እንዲሁም ቀኑ ለሚያመጣውን አዲስ ታሪክ በስሜት ይዘጋጃሉ።
ነገር ግን የመልኮሚያ እምብርት — ሁሉም ታሪክ የሚጀምርበት ቦታ — ሉማ ነች። ሉማ በመንደሩ መሃል የቆመችው፣ ባለ ረጅም ዕድሜ ፣ ወፍራም፣ የእናትነት ባህርይ ያላት ዛፍ ነች። ከሥሯ በታች በቀስታ በሚያንጸባርቁ ሥሮች እና እንደሚያጽናኑ በሚወዛወዙ ቅርንጫፎች፣ ሉማ የትውልዶችን ትውስታዎች ትይዛለች። እያንዳንዱ ሥር ታሪክ ይዟል። እያንዳንዱ ቅጠል ሹክሹክታን ይሸከማል። እና በቅርንጫፎቿ በኩል የሚነፍሰው እያንዳንዱ ነፋስ ሊታወቅ የሚጠብቅ ትምህርት ነው።
በሉማ ቅርንጫፎች ላይ መኖርያዋን ያረገችው ጓደኛቸው ደሞ ሊሎ የተባለችው ብሩህ የአቢሲኒያ የፍቅር ወፍ (lovebird) ናት። ሊሎ ከአህጉራት በሚያደርጉት ረጅም ጉዞ ወደ መልኮሚያ የሚያልፉ ብዙ ተጓዥ ወፎችን በመቀበል ከቅርንጫፍ ወደ ቅርንጫፍ ትበርራለች። እነዚህ ተጓዦች — ክሬኖች፣ ርግቦች፣ ዋጦች፣ ጅግራዎች እና ከኮረብታዎች ርቀው ከሚገኙ ምድሮች የመጡ ጥቃቅን መንገደኞች ከበረሃዎች፣ ከጫካዎች፣ ከውቅያኖሶች እና ከተራሮች የሰበሰቧቸውን ታሪኮች ለሊሎ ያካፍሏታል።
የፒቡ አስማት የሚጀምረው እዚያ ነው።
አዲስ ታሪክ ሲደርስ፣ ፒቡ እና ቀዮ ወደ ሉማ ይጣደፋሉ፤ አንዳንድ ጊዜ አሁንም በጭቅጭቅ መካከል፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በደስታ ትንፋሽ እያጠራቸው። ሉማ የወፉን ተረት ታዳምጣለች፣ ቅጠሎቿም በቀስታ ይደምቃሉ። ከዚያም በሞቀ ሽውታ፣ ታሪኩን ለፒቡ እና ለቀዮ ታቀርባለች።
ፒቡ በሉማ አጠገብ ተንበርክካ እጇን በሚያንጸባርቅ ሥር ላይ ታደርጋለች — ይህም ከባህሏ፣ ከ ማንነቷ፣ ከቅድመ አያቶቿ ታሪክ እና ከምድር ጥልቅ ጥበብ ጋር የሚያገናኛት ምልክት ነው። ከዚያም ሉማ አንድ የሚያብረቀርቅ ቅጠል ዝቅ ታደርጋለች። ፒቡ ቅጠሉን በጣቶቿ መካከል በቀስታ ታሻለች፣ እና በዙሪያዋ ያለው ዓለም መለወጥ ይጀምራል።
ቀለማት ይሽከረከራሉ።
ነፋሶች ይዘምራሉ።
ብርሃን ይጨፍራል።
እና በድንገት በፀጥታ — ወደ ታሪኩ ውስጥ ትገባለች።
ቀዮ ከእሷ ኋላ ወዲያውኑ ዘልሎ ይገባል — አንዳንድ ጊዜ በድፍረት፣ አንዳንድ ጊዜ በግዴለሽነት፣ እና አንዳንድ ጊዜ አሁንም እየተከራከረ። አብረው፣ ወደ ተረቱ ልብ ይገባሉ፣ ይማራሉ፣ ይመረምራሉ፣ ይሰናከላሉ፣ ይስቃሉ፣ እና ሁልጊዜም ከመንፈራገጡ በታች የተደበቀውን ትርጉም ያገኛሉ።
ጉዞው ሲያልቅ፣ ፒቡ እና ቀዮ ወደ መልኮሚያ ይመለሳሉ። ሉማ በቅጠሎቿ ሽውታ ፈገግ ትላለች። ሊሎ በደስታ ትጮሃለች። እና ፒቡና ቀዮ ከታሪኩ የተማሩትን ትምህርት ይወያያሉ።
ወደ መልኮሚያ እንኳን ደህና መጣችሁ — ሥሮች ትውስታን የሚሸከሙበት፣ ቅጠሎች ጥበብን የሚሹክሹኩበት፣ ተጓዥ ወፎች ከመላው ዓለም ታሪኮችን የሚያመጡበት፣ እና ፒቡ የተባለች ትንሽ ልጅ ትልቁ ጀብዷ የሚጀምረው በማወቅ ጉጉት መሆኑን የምታስታውሰን ቦታ ነው።
ይህ ገና መጀመሪያው ነው።
ተጨማሪ ታሪኮች በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የፒቡን ታሪኮች ለመከታተል የዩቲዩብ ቻናላችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ።
